የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር ) የአፍሪካ ህፃናት መብት ደህንነት ኮሚቴ ሊቀመንበርና የልዑካን ቡድናቸውን ተቀብለው አነጋግረዋል ።
በውይይቱ ሚኒስትሯ እንደገለፁት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የህፃናት መብትና ደህንነት ቻርተርን ተቀብለው ካፀደቁ 51 ሀገራት መካከል መሆኗን ጠቅሰው ይህም እንደሀገር ለህጻናት ሁለንተናዊ መብት መከበርና ማህበራዊ ደህንነት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን ማሣያ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለነዚህ ስምምነቶች አፈጻጸምና ስኬታማነት እገዛ የሚያደርጉ በርካታ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የተጣለባትን ሃገራዊና አህጉራዊ ግዴታና ሃላፊነት ለመወጣት ያለሳለሰ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
እንደሀገር ህፃናትን የሚመለከቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ከነዚህም መካከል የህፃናት የትምህርት ቤት ምገባ፣ የማህበረሰብ የህፃናት ማቆያና ሌሎችም እንደሚገኙበት ገልፀዋል። ኢትዮጵያ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል እና ለማስቀረት ተምሣሌት የሚሆን ስራ መስራቷን ገልፀዋል።
የአፍሪካ ህፃናት መብት ደህንነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ክቡር ዊልሰን አዳዎ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በህጻናት ሁለንተናዊ መብት መከበርና ማህበራዊ ደህንነት መረጋገጥ የሰራችውን ስራ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ እንድትሰጥ ጠይቀዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀደምትና ተምሣሌት ከሆኑ ሀገራት መካከል እንደሆነች ጠቅሰው በዚህም ኮሚቴው የህፃናት መብት መከበር፣ የህፃናት ተሳትፎና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ አህጉራዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀጥል እገዛ እንድታደርግ ጠይቀዋል።