የስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራ ተቋማዊነትን ለማጠናከር በተቀረፀው አዲስ የፕሮጀክት ኢኒሼቲቭ ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ተካሄደ።
በውይይቱ ላይ የኢፌዲሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የዩ ኤን ውመን ሀገራዊ ፕሮግራም አስተባባሪ ማዳም ሲሲል ሙካሩቡጋ እንዲሁም የዩኤን ኤፍ ፒ ምክትል ሀገራዊ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ታዎ ኦሉዮሚ እና የስፖኒሽ ኮርፖሬሽ ኤጀንሲ ዋና ሀላፊ ማሪዮ ፋንጁል ቤኒቴዝ ተሳትፈዋል። የኢፌዲሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ለስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ተቋማዊ የአሰራር ማዕቀፎችን በመቅረፅ በስራ ላይ ማዋሉ ገልፀዋል።
ሆኖም የስርዓተ ፆታ ጉዳይን ተቋማዊ በማድረግ በፌዴራል እና በክልል ደረጃ በአስፈፃሚ አካላትና ተቋማት በኩል የእውቀትና ክህሎት ክፍተት፣ የመረጃ እጥረት፣ የቁሳቁስና መሠረተ ልማት አለመሟላት እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራሩ ባለመጠናከሩ የሚፈለገው ውጤት ሊመዘገብ አለመቻሉ ጠቁመዋል። በጋራ ለመተግበር የተቀረፀው አዲሱ ፕሮግራም በዋነኝነት በስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራ ዙሪያ የሚሰሩ አስፈፃሚ አካላትን እና ተቋማትን አቅም የበለጠ በማጠናከር የዜጎችን /የሴቶችንና ልጃገረዶችን/ ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል ያለመ መሆኑ ተገልጿል። እንደሀገር ጠንካራ የአሰራር ሰርዓት ለመዘርጋት፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ተልዕኮን በአግባቡ እንዲወጡ ፕሮጀክቱ ያግዛል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በዩ ኤን ውመን፣ በዩኤን ኤፍ ፒና በስፖኒስ ኮርፖሬሽን ኤጀንሲ ትብብር ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ከክልል ሴክተር መዋቅር ጋር በመቀናጀት የሚገበር እንደሆነም ተመላክቷል። የፕሮጀክቱ ትግበራ በዚህ አመት ለማስጀመር መታቀዱንና የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ ሀብት ማሰባሰብ እንደሚገባም ተወያይተዋል። ለዚህም የበለጠ ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊነት ላይ የስራ ሃላፊዎቹ ተስማምተዋል።